Search Property

>

ሱማሌ ተራ የንግድ ማዕከል
2006ተመሰረተ

8/01/2020

ከቤት ውስጥ ሆኖ ለመስራት እንዴት ይቻላል?

የኮሮና ቫይረስ በአስደንጋጭ ፍጥነት መስፋፋትና መሰራጨቱን እንደቀጠለ ነው፡፡ ከቻይና ጥቂቶችን በማጥቃት የጀመረው ቫይረስ ዛሬ ላይ አለምን ሙሉበሙሉ በሚባል ደረጃ አዳርሷል፡፡ ሺወችንም ለበሽታና ለሞት ዳርጓል፡፡

የበሽታው መስፋፋትና መሰራጨትን ይበልጥ አስደንጋጭ ያደረገው ደግሞ እስከአሁን ምንም አይነት የመከላከያ ክትባትም ሆነ የመፈወሻ መድሃኒት ማግኘት አለመቻሉ ነው፡፡

የአለም የጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን በአለምአቀፍ ደረጃ መሰራጨቱን በመግለጽ አገራት በሽታውን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚረዱ መንገዶችን እንዲገብሩ መመሪያወችን አስቀምጧል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት በሽታውን ከመሰራጨት ለመከላከል ይረዳሉ ብሎ ያስቀመጣቸው ከሌሎች ጋር ያለንን ንኪኪ ማስወገድና ማህበራዊ ርቀት መጠበቅ ሳልና ማስነጠስ ሲኖረን በሶፍት ወይም ክንዳችንን በመጠቀም እንዲሁም በተቻለ መጠን ከእንቅስቃሱወች ተገድበን በየቤታችን እንድንቀመጥ ነው፡፡

አገራትም እነዚህን የመከላከያ እርምጃወች ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የተለያዩ ስልቶችን ቀርጸው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የትምህርት ተቋማትን ከመዝጋት ጀምሮ የመንግስት ሰራተኞችም በየቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ በመንግስት በኩል ተወስኖ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

ሰራተኞች በየቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መደረጉ ሰራተኞች ወደ መስሪያ ቤታቸው ሲሄዱ በትራንስፖርትና መንገዶች ላይ ያለውን መጨናነቅና የበሽታውን መሰራጨት ከማስቀረቱም በላይ በየመስሪያ ቤቱም የሚኖረውን መጨናነቅ ያስቀራል፡፡

ይሄን የመንግስትን ውሳኔ ተከትሎ በየቤታቸው ሆነው መደበኛ ስራቸውን እየሰሩ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በየቤታቸው ሆነው ለመስራት እንደተቸገሩ ለማስተዋል ይቻላል፡፡ ዛሬ እኛም ለቴክኖሎጂ አምዳችን ተከታታዮች በቤታችን ሆነን ለመስራት የሚያስችሉንን መንገዶችና ስልቶች ከዚህ እነደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡ መልከም ንባብ፡፡

እራስዎን ይጠብቁ

የሚጀመሪያው ነገር “እድለኛ” መሆንዎን ደጋግመው ለራስዎ ይንገሩት፡፡ ብዙ ሺዎች በዚህ በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ ሞተዋል፡፡ እርስዎ ግን በህይወት አሉ፡፡ ስለዚህ ፈጣሪዎን ሊያመሰግኑት ይገባል፡፡

ለበሽታ ሊያጋልጥዎት ከሚችል ማንኛውም ነገር ሁሉ እራስዎንም ሊጠብቁ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ እራስዎን መጠበቅ የሚገባዎት ከኮሮና ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም አካላዊና አእምሮአዊ እክል ሁሉ እራስዎን ሊጠብቁ ይገባዎታል፡፡ እዛው ቤትዎ ውስጥ የተለያዩ አካላዊ እንቅስቃሴወችንም ያድርጉ፡፡

ምቹ የስራ አከባቢን መፍጠርና ማዘጋጀት

ከዚህ በፊት በቤትዎ ውስጥ ሰርተው የማያውቁ ከነበሩ ለስራዎ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ማዘጋጀት፡፡

ü  ከስራ ባልደረቦችዎ ጋር የሚገናኙበትን የቴክኖሎጂ መንገድ ማዘጋጀት (ስልክ፤ ኢንተርኔት)

ü  ለስራ የሚያስፈልግዎትን የጽህፈት መሳሪያና ቁሳቁሶች ማዘጋጀት

ü  ምቹ ወንበር፤ ጠረንጴዛ የመሳሰሉትን ማሟላት

በየመሀሉ ረፍት ይኑርዎት

እራስዎን አግልለዉ እንዲቆዩ በሀኪም ተነግሮዎት ካልሆነ በስተቀር ቀኑን ሙሉ የስራ ክፍልዎ ውስጥ ባያሳልፉ ይመረጣል፡፡ በየተወሰነ ጊዜ (በመሃል በመሃል) እራስዎን ዘና እያደረጉና ከቢሮዎ ወጣ እያሉ ንጹህ አየር መቀበልና መንቀሳቀስ ይኖርብዎታል፡፡ እዚህ ላይ መንቀሳቀስ ሲባል ግን ከቤትዎ (ግቢዎ) ወጥተው መሄድ ላይኖርብዎት ይችላል፡፡ እዚያው ግቢ ውስጥ መንቀሳቀስ (ሰውነትን ማፍታታት) በቂ ነው፡፡

ከቤትዎ ሆነው ለመስራት የሚያስችልዎትን ህግና ደንብ ያዘጋጁ

በቤትዎ ውስጥ ሆነው ሲሰሩ ኑሮዎ እና የስራ ህይወትዎ እየተቀላቀለ እንዳያስቸግርዎ የሚረዳዎትን ህግ ያዘጋጁ፡፡

ü  እንደ ቢሮ የሚጠቀሙበትን የቤትዎን ክፍል ይወስኑ፡፡ ተጨማሪ ክፍል ከሌለዎት እንኳ የቤትዎ ጥግ ላይ ጠረንጴዛና ወንበርዎን በቢሮነት ለመገልገል ይወስኑ፡፡

ü  የስራ መግቢያና መውጫ ሰአትዎን ይወስኑ፡፡

ü  ከስራ ቦታዎ ውጭ ሆነው ለመስራት አይሞክሩ፡፡ ለምሳሌ ሶፋ ላይ ሆነው ስራዎን እየሰሩ እዚያው ቴሌቪዥንም የሚከታተሉ ከሆነ ስራዎን በአግባቡ ለመስራት ይቸገራሉ፡፡

በመሆኑም የስራ ቦታዎን እንዲሁም ስራ የሚሰሩበትን ግዜ እንዲሁም የሚዝናኑበትን ጊዜ ቀድመው መወሰን ይኖርብዎታል፡፡

ከስራ ባልደረቦችዎ (መስሪያ ቤትዎ) ጋር ሪፖርት ይለዋወጡ

ከመስሪያ ቤት ሲሰሩ ቆይተው በድንገት የስራ ቦታውን መቀየር የስራ ስሜቶ ላይ የሚፈጥረው አዲስ ስሜት መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ አዲሱን የስራ ቦታዎን እስኪለምዱት ድረስ ደግሞ ስራዎትን በአግባቡ ለመስራት እንደሚቸገሩ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ከስራ ባልደረቦችዎና የቅርብ አለቃዎ ጋር በየቀኑ ምንምን እንደሰሩ መልእክት (መረጃ) የምትለዋወጡበትን ጊዜ ማመቻቸት እና ግብረመልስ መቀያየር ጠቃሚና አጋዥ ነው፡፡

የድብርትና ብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማዎት ያድርጉ

ከበሽታው መስፋፋትና መሰራጨት ተከትሎ ብዙዎች ላይ እየደረሰ ካለው አካላዊ ጉዳት ባልተናነሰ (እንደውም በበለጠ) ዜጎች ላይ እየፈጠረ ያለው አእምሮአዊ ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡

እራስዎን ማረጋጋትና “የተሻለ ጊዜ ይመጣል” የሚለውን ለራስዎ መንገርን እንዳይዘነጉ፡፡ በተጨማሪም የሚሰማዎትን የብቸኝነት ስሜት ቀለል ሊያደርጉልዎት ከሚችሉ ሰዎች ጋር በስልክ ይደዋወሉ፡፡ እርስ በርስም ብርታትን መለዋወጥ አጋዥ መንገድ ነው፡፡ በጣም ፍርሀትና አሉታዊ ስሜት ከሚያጋሩዎት ወዳጆችዎ ጋር ለጊዜው ያለዎትን ግንኙነት ገታ ያድርጉት፡፡

የእንቅልፍ ጊዜዎን አይጨምሩ

እስከዛሬ የስራ ቦታዎ ላይ በሁለት ሰአት ለመድረስ ከአልጋዎ ላይ 12 ሰአት ላይ መነሳት ከነበረብዎት አሁን ላይ ግን ወደ ስራ ለመሄድ ያስፈልግዎ የነበረው አንድ ሰአት ስለቀረልዎ ይሄን ትርፍ ጊዜ ወደ እንቅልፍ ጊዜዎ ላይ አይጨምሩት፡፡ እስከዛሬ ይነሱ በነበረበት ጊዜ መነሳትዎን ይቀጥሉ፡፡ ይሄ ተግባር ለራስዎ በስራ ላይ እንዳሉ እንዲሰማዎ ስለሚያደርግ መነቃቃትዎን እንዳለ ይቀጥልልዎታል፡፡ ስለዚህ አላርምዎን እንዳይቀይሩ በተለመደው ጊዜ ይነሱ - እስከዛሬ ለመንገድ ይጠቀሙት የነበረውን ጊዜዎን አንዳንዱ ነገሮችን ለመተግበር ሊጠቀሙት ይችላሉ፡፡ ዜናወችን መከታተል - የሰውነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

በመጨረሻም እራስዎን እንዲጠብቁ በድጋሜ ለማሳሰብ እንዎዳለን መልካም ጊዜ፡፡